የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግጋትና መርኆች በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የጦር ሜዳ ውሎዎችና ውሳኔዎች ውስጥ የነበራቸው ቦታ

  • ነጋ እውነቴ መኮንን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት የሕግ ረዳት ፕሮፌሰር

Abstract

በኢትዮጵያ የተደረጉ ጦርነቶችን፣ የነገሥታት የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውሳኔዎችን አስመልክቶ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የውጭ አገር ጻሕፍት በአብዛኛው በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ ይህም የነገሥታት ፍርዶች በተለይም የጦር ሜዳ ውሎዎች በጭካኔ የተሞሉና ኢሰብአዊ እንደሆኑ አድርገው ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡1 በታሪክ ወደኋላ መለስ ብለን የአውሮፓዊያንን የጦር ሜዳ ታሪክ ብንፈትሽ እጅግ በጣም አስቀያሚና ዘግናኝ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ የሩቁን ትተን በአንጻሩ የቅርቡን እ.አ.አ. በ1859 ዓ.ም በፈረንሳይ፣ ሰርዲኒያና ኦስትሪያ መካከል የተደረገውን የሶልፈሪኖ ጦርነት አንኳ ብንወስድ አሰቃቂነቱንና ኢሰብአዊነቱን ከሄነሪ ዱና ማስታወሻ በሚገባ አንረዳለን፡፡ A Memory of Solferino የሚለውን መጽሐፍ ያነበበ ጦርነት ይረግማል እስኪባል ድረስ የሶልፈሪኖ ጦርነትን አሰቃቂነት ሄነሪ ዱና ጽፏል::2 የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር እንዲቋቋም የታሪክ አጋጣሚ እንዲፈጠር በዋናነት አስተዋጾ ያደረገውም ይህ ጦርነት ነው፡፡3 በኢትዮጵያ ርስበርስም ይሁን ከውጭ ወራሪ ጋር የተደረጉ ጦርነቶች ዘግናኝ የሆኑና የሰው ልጅን ለከፋ መከራ የዳረጉ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ርህራሄን መሠረት ያደረጉ፣ አስተዋይነት የተሞላባቸው፣ ለሰው ልጅ ክብር የሰጡ የነገሥታት የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውሳኔዎችን እናገኛለን፡፡
ጦርነትን ጨምሮ ትላንት የተፈጸመ አንድ ነገር መመዘንና መለካት ያለበት በዛሬ አስተሳሰብ፣ አስተምህሮ፣ መስታውትና ሕግ መሆን የለበትም፡፡ ሁሉም ትላንት የሆነ ነገር መታየት ያለበት በራሱ በትላንት ዐይንና አስተሳሰብ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አውሮፓዊ መሠረት ያላቸው ዘመናዊዎቹ የሰብአዊነት ሕግጋትና የጦርነት መርኆች ሥራ ላይ ከመዋላቸው በፊት ኢትዮጵያዊያን ነገሥታት የሰጧቸው ፍርዶችና በጦርነት ጊዜ የወሰኗቸው ውሳኔዎች ከእነዚህ ዘመናዊ ሕግጋትና መርኆች ጋር ተመሳሳይና ሰብአዊነትን አጉልተው የሚያሳዩ ነበሩ፡፡
ስለዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ብዙ ነገሮች በብዙ ጻሕፍት ተጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዘመነመሣፍንት ሰፍኖባት4 ከሰባ አመታት በላይ ማዕከላዊ መንግሥት አልባ ሆና ከቆየች በኋላ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲኖራት ያደረጉ፣ በቀን ከሌት ህልማቸው አውሮፓዊ ስልጣኔ በአገራቸው አውን ሆኖ ማየትን የተመኙ፣ የሰለጠነና በደመወዝ የሚተዳደር ዘመናዊ ወታደር ለማደራጀት የጣሩ፣ መንገድ የሰሩ፣ የባሪያ ንግድን ለማስቀረት የሞከሩና ሌሎች ከእሳቸው በፊት ያልተሞከሩና ያልታሰቡ ተግባራትን የሞከሩ ንጉሠነገሥት እንደነበሩ በሰፊው ተጽፏል፡፡5 በዚህ ፋና ወጊነታቸውም ከዘመናቸው ቀድመው የተፈጠሩ በማለት ብዙዎች አሞካሽተዋቸዋል፡፡
ምንም እንኳ ይህንና ሌሎች ተመሳሳይ አድናቆትና ሙገሳዎች ቢቸሯቸውም በአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ላይ የጻፉ ጻሕፍት አንድ አቢይ ጉዳይ ያመሳስላቸዋል፡፡ ይህም ንጉሠነገሥቱ ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ካለፍርድ ሰዎችን የገደሉ፣ የሰቀሉ፣ ወደገደል የወረወሩ፣ ቤት ዘግተው ያቃጠሉና ሌሎች ሰቆቃዎችን በሕዝባቸው ላይ የፈጸሙ በማለት ይወቅሷቸዋል፡፡ በተቃራኒው ንጉሠነገሥቱ የሰሯቸውን በጎ ተግባራት ማለትም ደግነታቸውን፣ ሩህሩህነታቸውን፣ ለጋስነታቸውን፣ በሕግና በፍርድ መሠረት መቅጣታቸውን አጉልቶ የጻፈ የሕግም ይሁን የታሪክ ምሁር አልተገኘም፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ጊዜ የሚወስድ ጥልቅ የታሪክና የሕግ ምርምር የሚጠይቁ ቢሆኑም በንጉሠነገሥቱ ዙሪያ ከተጻፉ የታሪክ መጻሕፍትና መድብሎች የዚህ ጥናት አቅራቢ የተረዳው ነገር ቢኖር አጼ ቴዎድሮስ ጨካኝና ካለፍርድ ሰዎችን የገደሉ ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ የጦር ሜዳ ውሎዎቻቸውና ውሳኔዎቻቸው ከዛሬዎቹ ዘመናዊ የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ (International Humanitarian Law) መርኆች ጋር ተቀረራቢ፣ ተመሳሳይና አቻ መሆናቸውን ነው፡፡

Downloads

Download data is not yet available.
Published
2016-06-01