በብሌን (1982) የፍቅር እስከ መቃብር “ስሑት አስተያየቶች” ላይ ሒሳዊ ፍካሬ

  • Gezahegn Tsegaw Aksum University

Abstract

ይህ ሒሳዊ ፍካሬ÷ ፍቅር እስከ መቃብርን አስመልክቶ በብሌን (1982) ወይይት ላይ የሥነ ጽሑፍ መምህራኑን (የዘሪሁን እና የደበበን 1982) ዕይታዎች መነሻ ያደረጉ ሦስት ጥቃቅን ሁነቶችን መዞ÷ ለመነሻዎቹ ጥያቄያዊ ሐቲቶች ምላሽ ለማርቀቅ ሞክሯል፡፡ ሒሳዊ ጥናቱ÷ ሦስቱን ገጸባህርያት ማንጸሪያ ያደረጉ ተናጠላዊ ሁነቶች ለመፈከር÷ በዮናስ (1992) ጥናት ላይ ተግባራዊ ከሆኑ የመፈከሪያ ሥልቶች ጋራ፣ የአንባቢ ምላሽ ሒስን (Reader-Response Criticism) አግባብቶ፣ በፊት ለፊት ከሚነገረን ጀርባ ያለን “ትርጉምና አንድምታ (meaning and significance) ፈልፍሎ ማውጣት” የሚያስችልን የፍካሬ (interpretation) ሥልት ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በፍካሬ ሂደቱም÷ አንደኛ፡- ሰብለ በዛብህን÷ “በፍቅር ጓደኝነት የተቆራኘችው የባላባት ዘር ሲነፍጓት፣ አማራጭ ስታጣ ነው” የሚለው የሐያስያኑ ምልከታ÷ የሰብለንም ሆነ የልቦለዱን ዐውዶች ያላገናዘበ÷ ርዕዮተ ዓለማዊ ወገንተኝነት የተጫነው “ስሑት አስተያየት” መሆኑን፤ ሁለተኛ፡- የፊታውራሪ መሸሻን ከፈረስ ላይ ወድቀው መሞትን ከግላዊ ባህርያቸው የሚመነጭ ተምሳሌታዊ ሞት በማድረግ ሀዲስ የተሳካላቸው መሆኑን፤ ሦስተኛ፡- የካሣ ዳምጤ “ጉድ” መባል አስመልክቶም÷ ደራሲው የገጸባህርይውን አፈንጋጭነት በውል የተገነዘቡ መሆናቸውንና በማፈንገጡ ጥያቄ እንዳያስነሳ “ጉድ” ብለው ለመሰየም መብቃታቸውን፤ ሒሳዊ ጥናቱ÷ በበቂ አስረጆች ለማጠየቅና ለመፈከር ሞክሯል፡፡ ፍቅር እስከ መቃብርም እንዲሁ ላይ ላዩን ብቻ ተነቦ የሚተነተን ሳይሆን÷ እያንዳንዱን ቅንጣት አሀድ በተናጠልና በጥቅል እያነበቡና እየመረመሩ የሚፈክሩት “የሐሳቦች ልቦለድ” መሆኑን÷ ይህም ሒሳዊ ጥናት መጠቆም ይወዳል፡፡

Downloads

Download data is not yet available.
Published
2022-07-28