Articles
የሰብአዊነት አሣሣል በዐፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል እና በበዓሉ ግርማ የቀይ ኮከብ ጥሪ ውስጥ
- Journal Ethiopian Journal of Languages and Literature
- Issue Vol 14 (2018): Ethiopian Journal of Languages and Literature
- Published
- ISSN 1728-8010
Abstract
የአማርኛ ዘመናዊ ልቦለድ እድገት ከአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ልብ ወለድ ታሪክ (ጦብያ) በ1900 ዓ/ም መታተም በኋላ ጎላ ያለ የጭብጥም የቅርጽም ለውጥ አስመዝግቧል፡፡ በርካታዎቹ የዘመናዊነት ገጽታዎቹም የዚህን የሥነ ጽሑፍ ዘውግ አታቾች ትኩረት በተለያየ ደረጃ ስበዋል፡፡ ሆኖም፣ ለአማርኛው ልቦለድ የግእዙ ሥነ ጽሑፍ መሠረትነት ወይም ይህ የልቦለድ ዘውግ በእድገት ግሥጋሴውም ላይ ቢሆን ከግእዙ ጋር በምን ሁኔታ እንደሚወራረስ ለማሳየት የሚገባውን ያህል በተመራማሪዎች አልተፈተሸም፡፡ ይህ ጽሑፍ ለአብነት የዐፄ ሱስንዮስን ዜና መዋዕል (ከግእዝ ወደ አማርኛ የተተረጎመ) ከበዓሉ ግርማ የቀይ ኮከብ ጥሪ ጋር በማነጻጸር ከሥነ ምግባራዊ ሰብዓዊነት ጭብጥ አተራረክ አንጻር ሁለቱ ያላቸውን ተመሳስሎና ልዩነት ለማሳየት ይሞክራል፡፡ ሁለቱን ድርሰቶች ለማነጻጸር መንደርደሪያው ሁለቱም ትርክ መሆናቸው፣ የሚሥሉት እውነታ በምናብ የተዋዛ መሆኑ፣ ታሪካቸው በተወሰነ ደረጃ በተመሳሳይ ፖለቲካዊ መርሖች የተቃኘ መሆኑና የሁለቱም ደራስያን የፖለቲካ ሹመኞች መሆናቸው ነው፡፡ ጽሑፉ ለአምባገነን አገዛዝ የቅርብ ባለሟል የሆነ ደራሲ ድርሰቱን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ማዋሉ ከጥንት የተወረሰ የድርሰት ባህል መሆኑን በአንድ በኩል ቢያረጋግጥም በሌላ በኩል ግን የኅሊና ሙግት ያለበት ደራሲ የፕሮፓጋንዳውን ማርከሻ በተዘዋዋሪ ለአንባቢው የሚያቀርብበት ሰምና ወርቅ ቅኔ መሰል የአተራረክ ስልት እንዳለውም ከዜና መዋዕሉ ማስረጃዎችን በመጠቃቀስ ያሳያል፡፡