ሒሳዊ ቅኝት÷ በሰሎሞን ተሾመ፣ ፎክሎር፡ ምንነቱና የጥናቱ የትኩረት አቅጣጫ ላይ
Abstract
ይህ ሒሳዊ ቅኝት፣ የ ፎክሎር፡ ምንነቱና የጥናቱ የትኩረት አቅጣጫ (2007 ዓ.ም.) መጽሐፍን ይዘትና ቅርጽ በተጠኑ መለኪያዎች መዝኖ፣ ዋና ዋና የሚባሉ ውስንነቶቹን ለማመላከትና ማረሚያ ነጥቦችን ለመጠቆም ሞክሯል፡፡ ጥናቱ፣ ከሙያዊ መጽሐፍ ግምገማ ጋራ ተያይዞ ተመራጭ እንደሆኑ የታመነባቸው፣ ሦስት በይነ ዲሲፕሊናዊ ማንጸሪያዎችን (perspectives) ተጠቅሞ፣ ከአካዳሚያዊ ዐውዶች ጋራ እያናበበ ተንትኗል፡፡ በሂደቱም መጽሐፉ፣ በፎክሎር መሠረታዊ ፅንሰ ሐሳቦችና ንድፈ ሐሳቦች ላይ መፋለሶች እንደተከሠቱበት፤ ያጣቀሳቸው ማስረጃዎች፣ መረጃዎችና የመረጃ ምንጮች (መጽሐፉንም ሙያዉንም በሚፈታተኑበት ደረጃ) ትክክለኝነትና ተገቢነት እንደሚጎላቸው፣ እንዲሁም፤ የሙያዊ ቃላት መዘበራረቆች፣ የትርጉም ስሕተቶችና የሰዋስው ግድፈቶች የመጽሐፉን የቋንቋ አጠቃቀም ሁኔታ እንደሚያደነቃቅፉበት በበቂ አስረጂዎች ተረጋግጧል፡፡ ጥናቱ፣ ለሁሉም የመጽሐፉ ደካማ ጎኖች ማመሳከሪያና ማረሚያ የሚሆኑ ማስረጃዎችንና የመረጃ ምንጮችን ስለሚጠቁም፣ መጽሐፉን በማስተማሪያነትና በማጣቀሻነት በሚገለገሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች መካከል፣ አካዳሚያዊ ውይይቶች እንዲደረጉ፣ መጽሐፉም ሕጸጾቹን አርሞ የሚቀርብበት መንገድ እንዲመቻች መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቆም ሞክሯል፡፡