“ትራውማ” በመረቅ ውስጥ
Abstract
ይህ ጥናት በ2007 ዓ.ም. በታተመው የአዳም ረታ ልብ ወለድ፣ መረቅ ላይ በዘመናዊው “የትራውማ ንድፈ ሐሳብ” የታገዘ ንባብ በማድረግ የትውልድን የልቡና መታወክ (ትራውማ) ለመፈተሽ የሞከረ ነው፡፡ የትራውማ መፈጠሪያ ምክንያቶችና መከሰቻዎች፣ የተስተማሰሉባቸውን ትዕምርቶችና ገጸ ጽሑፋዊ አቀራረቦች በመመርመር ዘመኑን የመፈከር፣ ትውልድ ዘለል ቀውሶቹን የማሳየት ዓላማ አለው፡፡ በውጤቱ ሕማሙ ያስከተለው ጉዳት በግለሰብ ሳይወሰን ወደ ማህበረሰብ መዝለቁ ታይቷል፡፡ የጉዳቱን ሰንሰለት ያራዘሙና የትራውማን ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋጋሪነት ያሳዩ መንገዶች መኖራቸውንም ማጤን ተችሏል፡፡ መረቅ በመረጠው የትረካ ስልት እና በተገለገለባቸው ልዩ ልዩ ገጸ ጽሑፋዊ አቀራረቦች እንዲሁም ትዕምርቶች ትራውማን በወጉ ነድፎ ማሳየት የቻለ ነው፡፡ በእነዚህ ስልቶች አማካይነት ለገጸ ባሕርይዎቹ የሥነ ልቡና ጉዳትና ትግል ምስል በመፍጠር ረቂቁንና ውስብስቡን ሥነ ልቡናዊ ቁስል ተጨባጭ አድርጓል፡፡ በጥቅሉ መረቅ ዘመንና ትውልድ እየተሻገረ በመጣ ጥርቅም ትራውማ ልቡናቸው ታውኮ፣ ዛሬያቸውን በራሳቸው መልክና ጣዕም መኖር ያልቻሉ፣ በትላንትና ዛሬ መኃል ባክነው የቀሩ ገጸ ባሕርያት ሥጋና ነፍስ የነሱበት የዚያ ዘመን አንደበት መሆኑን ማሳየት ችሏል፡፡ የገጸ ባሕርያቱ ከዛሬ ይልቅ በትላንታቸው ተጠምደው መታየት የትውስታ አንድ (ሌላ) ጎን የሆነውን ኖስታለዥያ (nostalgia) ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ ለማጥናት ጋባዥ ሆኖም ይታያል፡፡