የሥርዐተ ማኅሌት ደረጃዎች እና ተምሳሌታዊ ውክልናቸው

  • ተስፋዬ ሞላ

Abstract

ሥርዐተ ማኅሌት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲን ከሚከናወኑ ሥርዐተ አገልግሎቶች አንዱ ሲሆን& እንደ መንፈሳዊ ጥበብነቱ የራሱ የሆነ ተምሳሌታዊ ውክልና አለው፡፡ ተምሳሌታዊ ውክልናው ጥበቡን መሠረት በማድረግ የሚከናወን አተረጓጐምና የአፈካከር (interpretation) ዘዴ ነው፡፡ ሥርዐተ ማኀሌት በንዋያተ መዝሙራት (ከበሮ፣ መቋሚያ እና ጸናጽል) ታጅቦ የሚከናወን መንፈሳዊ ሥርዐተ አገልግሎት ከመሆኑም ባሻገር የራሱ የሆኑ ፎክሎራዊ መገለጫዎች አሉት፡፡ እነዚህ ፎክሎራዊ መገለጫዎች ሥርዐተ አገልግሎቱን ደረጃዎችን በጠበቀ መልኩ ለማከናወን የሚያግዙና ለሥርዐቱ ተምሳሌታዊ ውክልና ጉልህ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ ሥርዐተ ማኀሌት በሦስት ምድቦች ማለትም የክብረ በዓል፣ የወርኀ በዓል እና የእሑድ በሚሉ ክፍሎች ተከፍሎ የሚከናወን መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሆን በውስጡ ዐሥር ደረጃዎች  የያዘ ነው፡፡ እነዚህም ደረጃዎች መቃኘት፣ መቀበል፣ መምራት፣ መመራት፣ ዝማሜ፣ ንዑስ መረግድ፣ ዐቢይ መረግድ ፣ ጽፋት ፣ድርብ ጽፋት እና የጭብጨባ ጽፋት ሲሆኑ ቅዱስ ዳዊት ወበዐሥርቱ አውታሪሁ መዝሙረ ማኅሌት ወመሰንቆ እዜምርለከ (ዐሥር አውታር ባለው መዝሙር እዘምርልሃለሁ ያለውን መሠረት በማድረግ እና ከዐሥርቱ ማዕረገ ጻድቃን ጋር ተያይዞ ተምሳሌቱ እንደሚገለጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የሥርዐተ ማኅሌት ደረጃዎች ተምሳሌታዊ ውክልና የቤተክርስቲያንን የአተረጓጎም ይትበሃል እና የሐዋርያትን አስተምህሮ መሠረት በማድረግ የተመሰሉ ሲሆን& ደረጃዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስን የነገረ መስቀል ድህነት የሚያብራሩ፣ የሚተነትኑ እና የሚያስረዱ ናቸው፡፡ የደረጃዎቹ ተምሳሌታዊ ውክልና የቤተክርስቲያንን ሥርዐተ አስተምህሮ መሠረት ያደረጉ ከመሆናቸውም ባሻገር ፎክሎራዊ የተምሳሌት ሳይንስን ያካተቱ ናቸው፡፡ በፎክሎር የክብረ በዓላት ጥናት አንድ ሥርዐተ ክዋኔ ደረጃውን ጠብቆ ሲከናወን የሥርዐተ ክዋኔው እውንነትና ህልውና የሚረጋገጠው በተምሳሌታዊ ውክልና ነው፡፡ ተምሳሌቱም ከሥርዐተ ክዋኔው የአከዋወን መስተጋብር እና ሥርዐተ አገልግሎት የሚመነጭ በመሆኑ በዘፈቀደ የሚፈከር አይደለም፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲን ሥርዐተ ማኅሌት በሚገባ ለመገንዘብ የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርተ ሃይማኖት፣የሐዋርያትን አስተምህሮ እና የተምሳሌት አሰጣጥ ዘዴ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውቀትን በእጅጉ ይጠይቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፎክሎራዊ የተምሳሌት ይትበሃልን መገንዘብ ሌላኛው ሥርዐቱን ለማወቅ የሚያግዝ ክህሎት ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

Downloads

Download data is not yet available.
Published
2012-08-20