SELECTED SOTERIOLOGICAL THEMES IN SAINT YARED’S HYMNS OF THE SABBATH

  • Tsehaye Dedimas

Abstract


አጠቃሎ
“ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት” እየተባሉ ከሚጠሩት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት አንዷ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተለያዩ ቋንቋዎች ከተረጐመቻቸው በርካታ መጻሕፍት በተጨማሪ
በራሷ ሊቃውንት የተደረሱ አያሌ መጻሕፍት ባለቤት ናት። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ነገረ መለኮታዊ አስተምህሮዎችን ሲያፈላልግ ከቅዱስ ያሬድ መጻሕፍት በተለይም ከድጓ የተሻለ ማረፊያ አላገኘም። የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማም ቅዱስ ያሬድ በመጻሕፍቱ ያስቀመጣቸውን ነገረ ድኅነታዊ አስተምህሮዎች መፈለግና ነገረ ድኅነታዊ አገላለጾቹን ማሳየት ነው። ወደዚህ ግብ ለመድረስም ጸሐፊው የቅዱስ ያሬድ ምስጋናዎች ነገረ ድኅነታዊ ፋይዳ አላቸውን? ካላቸውስ ቅዱስ ያሬድ ነገረ ድኅነትን እንዴት ነው የገለጸው? ነገረ ድኅነታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጾችንስ እንዴት ነው የተረዳቸውና የተረጐማቸው? አስተምህሮዎቹስ ከሌሎች ሊቃውንት ነገረ መለኮታዊ እሳቤዎች ጋር ይስማማሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች አንሥቷል። ከዓላማው ለመድረስ ደግሞ የዘማሪውን ነገረ ድኅነታዊ አእምሮ እንደሚያሳዩ በማመን ከድጓው መጽሐፍ የሰናብትን (የእሑዶችን) መዝሙራት ብቻ በመምረጥ ነገረ መለኮታዊ ይዘታቸውን መርምሯል። አቅራቢው መጀመሪያ ከመዝሙራቱ ነገረ ድኅነታዊ ሐሳብ የያዙትን መዝሙራትና የመዝሙራት ክፍሎች በመምረጥና በመሰብሰብ ወደ እንግሊዝኛ የተረጐማቸው ሲሆን በመቀጠል ደግሞ የዘማሪውን ጽሑፎች ነገረ ድኅነታዊ አስተምህሮ ከአበው ጽሑፎችና በአበው ጽሑፎች ላይ ከተደረጉ ጥናቶች ጋር እያነጻጸረ መርምሯቸዋል። በመጨረሻም የቅዱስ ያሬድ መዝሙራት በዓላማቸው የእግዚአብሔርን ክብር ለመግለጽ የቅዱሳንንም ቅድስና ለማጉላት የተጻፉ ቢመስሉም በይዘታቸው ግን ከሚገመተው በላይ ነገረ ድኅነታዊ ሆነው አግኝቷቸዋል። ነገረ ድኅነታዊ አገላለጾቹም በብሉይ ኪዳን የተፈጸሙ እና የታዩ ምሳሌዎችን እና የተነገሩ ትንቢቶችን በመተርጎም ላይ የተመሠረቱ፣ ልዩ ልዩ ምልክቶችን በማተት ነገረ ድኅነትን የሚያጎሉ እና የራሱ በሆኑ አገላለጾች
የተሞሉ መሆናቸውን አረጋግጧል። በመጨረሻም ሦስት ወሳኝ ያላቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎች አቅርቧል፡፡ አንደኛ የቅዱስ ያሬድ የምስጋና ድርሰቶች ተመራማሪዎች በቀላሉ እንዲያገኟቸውና ለዓለም እንዲተዋወቁ (በተለይ ወደ
እንግሊዝኛ) መተርጐም አለባቸው። ሁለተኛ በውስጣቸው አምቀው የያዙት ጥበብ እንዲታወቅና ብዙ አንባብያን እንዲጠቀሙባቸው ይዘታቸውና አስተምህሯቸው በስፋትና በጥልቀት መመርመር ይገባቸዋል። በሦስተኛ ደረጃም መጻሕፍቱ
የ ቋጠሩትን ሀብት ለዓለም እንድናጋራው የዘማሪው ሥራዎች ትርጉሞችም ይሁኑ በዘማሪው ሥራዎች ላይ የሚደረጉ የምርምር ውጤቶች ለኅትመትእንዲበቁ መደረግ አለባቸው።

Downloads

Download data is not yet available.
Published
2016-04-10