Content analysis of Mäṣḥafä Mäwaśə’ət

  • Birhanu Akal

Abstract

አኅፅሮተ ጥናት
የዚኽ ጽሑፍ ዐላማ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ ትምህርት ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የዜማ ትምህርቶች መካከል አንዱ ስለኾነው መጽሐፈ መዋሥእት ትምህርታዊ ይዘት ማብራራትና ትንትኔ መስጠት ነው፡፡ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይኽንና ሌሎች የዜማ ድርሰቶችን ስለ ደረሰው ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ ጻድቁ አባ አረጋዊ እና ንጉሥ ገብረ መስቀል በወቅቱ የነበራቸውን ሀገራዊና ሃይማኖታዊ ፍቅር ያብራራል፡፡ እንዲኹም ድርሰቱ ስለተደረሰበትና ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ ቅዱሳን ሦስት ዐመት ስለተቀመጡባት ታላቋ ገዳም ዙር አምባ አረጋዊ ጽርሐ ዐርያም ያብራራል፡፡ በተጨማሪም ሊቃውንቱ መዋሥእትን እንዴት እንደሚማሩት እና እንደሚያስተምሩት ከጀማሪ ደቀ መዝሙር እስከ አድራሽ (ዕጩ መምህር) የትምህርት አሰጣጥ ሥልቱን ያስረዳል፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ከሌሎች የዜማ እና የንባብ መጻሕፍት ጋር ያለውን ልዩነት እና ተመሳሳይነት ታሪካዊ እና ሥነ ጽሑፋዊ ጠቀሜታ ማኅበራዊ መስተጋብር ያብራራል፡፡ በዋናነት ተመራማሪዎች በቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ይልቁንም በዜማ መጻሕፍት ላይ የበለጠ የዘርፉ ሊቃውንት እንዲመራመሩ መነሻ ይኾናል፡፡ መጽሐፈ መዋሥእት ምንም እንኳን በየሊቃውንቱ እጅ እና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በብዛት ቢኖርም ለዚኽ ጥናት የተመረጡት ግን አስፈላጊነታቸው ጉልህ ኾኖ የተገኙ ኹለት የብራና መጻሕፍት ብቻ ናቸው፡፡ አንደኛው በዙር አምባ ጽርሐ ዐርያም ገዳም በጉባኤ ቤቱ የሚገኝ በመጠን አነስ የሚል እና ሊቃውንቱ የሚማሩበት ነው:: ስሙም መዝገብ ይባላል፡፡ ምንም እንኳን ኹሉም አድራሾች የየራሳቸው መጻሕፍት ቢኖሩአቸውም ከፍተኛውን ዕውቀት ለማዳበር በዚኽ ይማራሉ:: ኹለተኛው ደግሞ በዚኽችው ገዳም ዕቃ ቤት የሚገኝ ሲኾን ሊቃውንቱ ከራሳቸው መጽሐፍ እና ከመዝገብ ያልተስተካከለውን ለማመሳከር የዕቃ ቤት ሐሓላፊውን እያስፈቀዱ አልፎ አልፎ ያዩታል:: በመጠንም ከመጀመሪያው ከፍ ያለ ነው:: ልዩ መጠረያ ስሙም መጽሔት ይባላል::

Downloads

Download data is not yet available.
Published
2017-08-10