Articles
አጠቃላይ የጽሕፈት ሥርዓትና የፊደል ዳሰሳ ትኩረት በኢትዮጵያ የፊደል ገበታ ላይ (Ethiopic Script)
- Journal ZENA - LISSAN (Journal of Academy of Ethiopian Languages and Cultures)
- Issue Vol 26 No 1 (2017): ZENA-LISSAN (Journal of Academy of Ethiopian Languages and Cultures)
- Published
- ISSN 2222-6028
Abstract
የጽሕፈት ሥርዓት መቼ እንደተጀመረ እና የት እንደተጀመረ በትክክል ባይታወቅም፤በጥንት ሰዎች የተሣሉ የዋሻ ውስጥ ሥዕሎች ለጽሕፈት መገኘት ምንጭ ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡ ለምሳሌ በሰሜን ስፔን አልታሚራ በሚባል ዋሻ ውስጥ የሚታዩ ሥዕሎችከዛሬ ሃያ ሺህ ዓመት በፊት በጥንታዊ ሰዎች እንደተሣሉና ዛሬም ድረስ እንደሚነበቡ ይነገራል፡፡ እነዚህ ሥዕሎችበወቅቱ የነበረውን የሕይወት ገፅታ የሚያሳዩ እንደሆኑም ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሥዕሎች ለምን ጉዳይ እንደተሣሉ የሚታወቅበት ዘዴም ሆነ መንገድ የለም፤ ምናልባትም ከመግባቢያ መሳሪያነት ይልቅ ለሥነ ውበት መግለጫ የተሣሉ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡(Fromkin & Rodman 1993፡364)፡፡
ለዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ መነሻ ምክንያት የሆነው ነገር በአሁኑ ጊዜ አገራችን ውስጥ ስለፊደል የተለያዩና አንዳንዴም ኢ-ስነልሳናዊ የሆኑ አመለካከቶች በስፋት ሲያንጸባርቁ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ አንዳድ ሰዎች ይሄ ፊደል የኛን ቋንቋ ሊጽፍ አይችልም፤ ምክንያቱም አያጠብቅም፤ አያላላም፤ ድምጸትን አያመለክትም[1] ወዘተ. ያኛው ፊደል ግን የኛን ቋንቋ ሊጽፍ ይችላል፤ ምክንያቱም ያጠብቃል ያላላል ወዘተ. በማለት ሲከራከሩ ይሰማል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰዎች የላቲን ፊደል ለኩሽና ለኦሞ ቋንቋዎች ብቻ፤ የኢትዮጵያው ፊደል ደግሞ ለሴም ቋንቋዎች ብቻ ተሰማሚና ምቹ ፈደሎች ናቸው ይላሉ፡፡ በመሰረቱ ማንኛውንም ቋንቋ በማንውም ፊደል መጻፍ ይቻላል[2]፡፡ ትልቁ ጉዳይ በአንጻራዊ መልኩም ቢሆን የትኛው ፊደል ለመማር ማስተማር ሂደት አስቸጋሪ ወይም ቀላል ነው የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልናስተውል የሚገባን ነገር፤ ሁሉም የጽሕፈት ሥርዓቶች ደካማና ጠንካራ ጎን እንዳላቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ በተለይ በአሁኑ ዘመን እየተሠራባቸው ባሉት ሦስቱ የጽሕፈት ሥርዓቶች (ቃላዊ፤ ቀለማዊና ንጥረድምጻዊ) መካከል ስላለው ችግር እና ጠቀሜታ ጠቅለል ባለና ንፅፅራዊ በሆነ መልኩ ለመዳሰስ ይሞከራል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት በሥራ ላይ የዋሉትን የኢትዮጵያ የጽሕፈት ሥርዓትና የላቲን የጽሕፈት ሥርዓትን ዘርዘር ባለ መልኩ ለማቅረብ ይሞከራል፡፡ ጠንካራና ደካማ ጎናቸው ላይም ጥናቱ ጥቆማ ያደርጋል፡፡