Articles
የዕድር የሃይማኖት መቻቻል መልኮች በበቆጂ ከተማ
- Journal ZENA - LISSAN (Journal of Academy of Ethiopian Languages and Cultures)
- Issue Vol 26 No 2 (2017): ZENA-LISSAN (Journal of Academy of Ethiopian Languages and Cultures)
- Published
- ISSN 2222-6028
Abstract
ዕድር በሀገራችን የተለመደና በተለይ የቀብር ስርዓት እና ተያያዥ ተግባራትን በመተጋገዝ
ለመከወን ተቀራርበው የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች በፈቃደኝነት የሚመሰርቱት ባህላዊ ተቋም
ነው። ዕድር በኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ለተመሳሳይ አላማ በየጊዜው የሚቋቋም
ታዋቂ ባህላዊ ተቋም ሲሆን በበቆጂ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ከ1941 ዓ.ም ጀምሮ የሚታወቅ
ተቋም ነው። በርእሱ የተጠቀሰው የጥናቱ ዋና ዐላማ በበቆጂ ከተማ አስተዳደር የተቋቋሙ
ዕድሮችን ምንነት በመግለጽ የተለያየ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ዕድርተኞች ተቻችለው የአንድ
ዕድር አባል በመሆን የሚኖሩበትን ዘዴ ከፎክሎር ጥናት አኳያ ይተነትናል። መረጃዎቹ በመስክ
በመገኘት በምልከታ፣ በቃለ-መጠይቅ፣ በቡድን ውይይት እና በሰነድ ምርመራ ዘዴ የተሰባሰቡ
ናቸው። በጥናቱ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች ተከታይ
ማህበረሰቦች ዕድሮችን በጋራ ይመሠርታሉ፡፡ አንድ ዕድር ሲመሰረት የሚቀራረቡ፣ ሰዎች
በፈቃደኝነት ተሰባስበው በተወሰነ ጊዜ በመገናኘት ገንዘብ በማዋጣት የሚመሰርቱት ተቋም ነው።
የሁሉም ዕድሮች ዋና አላማ አባሉ፣ የቅርብ ዘመዱ ፣ ቤተሰቡ ውይም እራሱ በሞት ሲለይ በተለያየ መልኩ
ሀዘንተኛው ለመርዳት ነው፡፡ ሁሉም ዕድሮች በጽሁፍ የሰፈረ መተዳደሪያ ደንብ አላቸው። ደንቦች የያዙት
ዋና ዋና ነጥቦች፡- የዕድሩን አላማ፣ በአባልነት የሚካተቱ ግለሰቦች ማሟላት ስለሚገባቸው መስፈርት፣
የአባላቱ መብትና ግዴታ፣ የዕድሩ አስተዳደር አካል ማንነት፣ መብትና ግዴታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን የያዘ
ነው። በዚሁ መሠረት አንድ የእድሩ አባል ወይም የቅርብ ዘመድ ሲሞት ዕድርተኛው፤ የሟችን
አስከሬን ወደ መቃብር በክብር በመሸኘት ከመቃብር መልስ እስከ ሶስት ቀን የሟችን የቅርብ
ዘመዶች በማጽናናት በጉልበት፣ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በመሳሰሉት ማገዝ ነው። የዕድሮቹ አደረጃጀት
በአንድ ሰፈር የሚኖሩ የመሰረቱት፣ የሰፈር ዕድር ሲባል ይህም የወንዶችና የሴቶች(ወይም የሴቶች
ባልትና) ተብሎይለያያል። በከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆነውን ሁሉ የሚያካትተው ትልቁ ዕድር
ይሉታል። በበቆጂ ከተማ ከ1982 ዓም በኋላ የዕድር ክፍፍል የእድሩ አባል በሚከተለው ሃይማኖት
ምክንያት ልዩነት አምጥቷል። ልዩነቱም የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች በአብዛኞቹ ዕድሮች
አባል መሆን አለመቻል ነው። በዕድርተኞች መካከል የሚከወኑ እሴቶች ደግሞ መቻቻል
ከሚያካትታቸው ባሕርያት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው ተቻችለው የሚኖሩ
የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች እንዳሉት ሁሉ አለመቻቻል የታየባቸው እንዳሉም ይጠቁማል።